ብድር

አዋጭ እስከ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ባለው ሪፖርት መሰረት ከ14.7 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ለ37,787 አባላቱ አሰራጭቷል።

የብድር አገልግሎት

አዋጭ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የብድር አገልግሎት ነው፡፡ ማንኛውም አባል ለብድር የሚጠየቁ ቅድመ መስፈርቶችን እስካሟላ ድረስ ብድር የማግኘት መብት አለው፡፡ ለዚህም  የህብረት ስራ ማህበሩ የብድር ኮሚቴ እና የብድር ክፍል አንድ አባል ብድር እንዲወስድ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችን በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡ በዚህም መሰረት ቅድመ ሁኔታውን ያሟሉ አባላት የሚያቀርቡትን የብድር ማመልከቻ የብድር ክፍል በማየትና በማረጋገጥ ለብድር ኮሚቴ አፀድቆ ለሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በማቅረብ ክፍያ እንዲፈፀም ያደርጋል፡፡ 

የብድር መስፈርቶች

 • ማንኛውንም አይነት ብድር ለመበደር ያሰበ አባል አባል ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ለተከታታይ 6 ወራት ሊበደር ያቀደውን ገንዘብ 1/4ኛውን ወይም 25 በመቶውን አስቀድሞ መቆጠብ ይኖርበታል፡፡
 • አንድ አባል የቤት ወይም የመኪና ብድር ለመውሰድ ሲፈልግ ቢያንስ በተከታታይ ለተከታታይ 6 ወራት የሚወስደውን የብድር መጠን 25% መቆጠብ ይኖርበታል፡፡  
 • ተበዳሪው ለመበደር ሲመጣ ተመጣጣኝ የሆነ ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዳለው የሚያሳይ ደብዳቤ/የሥራ ውል/የንግድ ሥራ ፈቃድ ይዞ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ 
 • ተበዳሪው የንግድ ብድር ለመውሰድ የታደሰ የንግድ ፈቃድ እና የሂሳብ እንቅስቃሴውን የሚያሳይ የባንክ ስቴትመንት ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ 
 • አንድ አባል ብድር ሲወስድ ከወሰደው ገንዘብ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ዋስትና ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
 • አንድ አባል ብድር ሲወስድ ከሚያቀርበው ተመጣጣኝ ዋስትና በተጨማሪ ከአባል አንድ ሰው ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
 • ተበዳሪው ብድር በሚወስደበት ወቅት አንድ ጊዜ የሚታሰብ የአገልግሎት 1% እና ከቀሪ እዳ ላይ በየአመቱ የሚታሰብ የኢንሹራንስ 1% በአጠቃላይ የብድሩን 2% ይከፍላል፡፡ 

የብድር መጠን

 • አንድ አባል ለማህበራዊ ጉዳይ፣ ለጤና፣ ለትምህርት እስከ 800 ሺህ ብር ብድር መውሰድ ይችላል፡፡
 • ለአነስተኛ ንግድ እስከ 1,000,000 (1 ሚሊዮን) ብር ብድር መውሰድ ይችላል፡፡
 • አንድ አባል ለቤት መኪና መግዣ እስከ 2,500,000 (2.5 ሚሊዮን) ብር ብድር መውሰድ ይችላል፡፡
 • አንድ አባል ለንግድ መኪና መግዣ እስከ 3,000,000 (3 ሚሊዮን)  ብር ብድር መውሰድ ይችላል፡፡
 • አንድ አባል ለቤት መግዣ፣ መስሪያ እና ማደሻ እስከ 5,000,000 (5 ሚሊዮን) ብር ብድር መውሰድ ይችላል፡፡

የብድር ወለድ

አባላት ለተበደሩት ገንዘብ እንደየብድሩ አይነት በዓመት ወለድ ይከፍላሉ፡፡ በዚህም መሰረት ለማህበራዊ እና ለንግድ ብድር 13.5 በመቶ ለወንዶች 13 በመቶ ለሴቶች ሲሆን ለመኪና መግዣ ብድር 14.5 በመቶ እንዲሁም ለቤት መግዣ፣ መስሪያና ማደሻ ብድር ደግሞ 15.5 በመቶ ወለድ በዓመት ይከፍላሉ፡፡ የወለድ አከፋፈሉም በየወሩ በቀሪ እዳ ላይ የሚታሰብ ይሆናል፡፡ 

የተሰጠ ብድር መጠን

አዋጭ የገ/ቁ/ብ/ኅ/ሥ/ማኅበር እስከ 2016 ዓ.ም. ድረስ ባለው ሪፖርት መሰረት ከ14.7 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለ37,787 አባላት የሰጠ ሲሆን አባላትም በተበደሩት ገንዘብ የራሳቸው መኖሪያ ቤት እና መኪና እንዲኖራቸው ከማስቻሉም በተጨማሪ የራሳቸው በሆነ አነስተኛ ንግድ ተሰማርተው የኑሮ ደረጃቸው እንዲሻሻል አድርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሴት አባላትን በተለያየ መንገድ በማበረታታት ብድር ወስደው የራሳቸውን ስራ በመስራትና የጀመሩትን ስራ በማስፋፋት ከድህነት ወጥተው ቤተሰቦቻቸውን እንዲደግፉ እገዛ አድርጓል፡፡ 

በአጠቃላይ የኅብረት ሥራ ማኅበሩ ባመቻቸው የብድር አቅርቦት ምክንያት ለ42,043 ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡ በዚህም ለአባላት በተሰጠው ብድር ምክንያት በተፈጠረው የስራ ዕድል በአማካይ 100,059 አባላትና የአባላት ቤተሰቦች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በአጠቃላይ እስከ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ

 • ለአባላት ከ1.3 ቢሊየን ብር በላይ ሼር/ዕጣ ተሽጧል፡፡
 • ከ9.1  ቢሊየን ብር በላይ ቁጠባ  ከአባላት ተሰብስቧል፡፡        
 • ከ14.7 ቢሊየን ብር በላይ ብድር  ለ37,787 አባላት ተሰጥቷል፡፡          

የቅርንጫፍ ቢሮዎች ብዛት

 • በአዲስ አበባ                                                16
 • በኦሮሚያ ክልል                                             9
 • በአማራ ክልል                                               1
 • በሲዳማ ክልል                                               2
 • በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል               1
 • በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል                                1
 • በደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል                         1
© Awach SACCoS. All rights reserved
Website By: Alen Teshome