The Honorable Commissioner of the Ethiopian Cooperative Commission Mrs. Freyalem Shibabau and her colleagues made a useful visit!

Start Date

የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮምሽን ኮምሽነር ክብርት ወ/ሮ ፍሬያለም ሽባባው እና የሥራ ባልደረቦቻቸው በአዋጭ የስራ ጉብኝት አደረጉ!

በወ/ሮ ፍሬዓለም ሽባባው የተመራው ልዑካን ቡድን አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅ/ሥ/ማህበር ዋና ጽ/ቤትን የጎበኙ ሲሆን በእያንዳንዱ የስራ ክፍል ውስጥ የሚከናወኑ ስራዎችና ያሉ የሥራ እንቅስቃሴዎች በየክፍሉ ኃላፊዎች ተገልጾላቸዋል፡፡ ከቢሮ ጉብኝት በኋላ በነበረው የውይይት መድረክ ላይ አጠቃላይ የአዋጭን የሥራ ሂደት፣ የደረሰበትን ደረጃ፣ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች እና በቀጣይ የሚሰራቸውን ስራዎች የሚያሳይ ገለፃ በአቶ ገረመው አማረ የተደረገ ሲሆን ከገለፃው በኋላ በቀጠለው ውይይት ላይ ክብርት ወ/ሮ ፍሬዓለም ካነሷቸው ሃሳቦች መካከል ህብረት ስራ ማህበራችሁ ከራዕዩ አንፃር ሴክተሩ የሚስፋፋበትን መንገድ ቢያፋጥነው ለዚህም እኛ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናችንን፣ አዋጭ የገበሬውን የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍ በግብርና ላይ የሚሰሩ ህብረት ሥራ ማህበራትን መደገፍና አብሯቸው መስራት እንዳለበት፣ የቦታ ጥያቄያችሁ መልስ ማግኘት ስለሚኖርበት በዚህ ጉዳይ ላይ ኮምሽኑ አሁንም ድጋፍ እንደሚያደርግ እና ለዚህ ምላሽ ለማግኘት አብረውን እንደሚሰሩ እንዲሁም ሀገራዊ የህብረት ሥራ ፌደሬሽን እና የህብረት ሥራ ባንክ መመስረቱ አስፈላጊ እና ብዙ ሃገራዊ ችግሮችን ሊቀርፍ ስለሚችል በዚህም ላይ አዋጭን ጨምሮ በትብብር መስራት ይኖርብናል የሚሉ ሀሳቦች አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ እነኚህኑ ሀሳቦችም በስፋት ለመወያየት የሚቻልባቸውንም ትልልቅ መድረኮች በቀጣይ በኮምሽኑ እንደሚዘጋጁ ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም ወ/ሮ ፍሬዓለም ሽባባው ይህን ተቋም በመጎብኘቴ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል የተወያየንባቸው የወደፊት ዕቅዶችን በጋራ ለመስራት እንተጋለን ያየነው መልካም መንፈስ እና ትጋት ሀገራችንን የመቀየር አቅሙ ትልቅ መሆኑን ተገንዘብቤያለሁ ብለዋል፡፡ በዚህም ጉብኝት ላይ የኮምሽነሩ ም/ኮምሽነር ክቡር አቶ አብዲ ሙመድ፣ የፅ/ቤቱ ኃላፊ አቶ አምባዬ እና ሌሎች የኮምሽኑ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአዋጭ የቦርድ አባላትም ተገኝተዋል፡፡

Event Images
© Awach SACCoS. All rights reserved
Website By: Alen Teshome