ወ/ሮ ብርቄ ወየቻ

From
ቢሾፍቱ
አዋጭ እንደስሙ አዋጭ ነው

/ሮ ብርቄ ወየቻ እባላለሁ ፡፡ ባለትዳር እና የሶስት ልጆች እናት ነኝ፡፡ ተወልጄ ያደኩት በቢሾፍቱ ከተማ ነው፡፡ ቢሾፍቱ ከተማ ማለት ከአዲስ አበባ አርባ አምስት ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ የምትገኝ ወደፊት በኢትዮጲያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ከሚያድጉ ከተሞች ተርታ የምትጠቀስ ከተማ ነች፡፡ ከተማዋ ለአዲስ አበባ በጣም ቅርብ ነች፡፡ በመኪና ከአርባ ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ነድተን መግባት እንችላለን፡፡ በተለይ ደግሞ በቱሪዝሙ በኩል በጣም እያደገች ያለች እና ከሌሎች መሰል ከተሞች በላይ ማደግ እንደምትችል ተስፋ የተጣለባት ከተማ ነች፡፡

አንድ ቀን በምንገድ ላይ ስሄድ አዋጭ በቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ያለው ቅርንጫፍ ቢሮ ላይ ያለውን ማስታወቂያ አይቼ ወደ ህብረት ስራ ማህበሩ ቢሮ ጎራ በማለት እና መረጃ በመጠየቅ የአዋጭ የህብረት ስራ ማህበር አባል ልሆን ችያለሁ፡፡ እንግዲህ አባል ከሆንኩ በኋላ ለተከታታይ ስድስት ወራት ቁጠባዬን በሚገባ በመቆጠብ ለምሰራው ስራ ማስፋፊያ ብድር አራት መቶ ሺህ ብር ጠየኩኝ፡፡ የምሰራው የልብስ ስፌት ስራ ነበር፡፡ በአጋጣሚ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሲገባ ስራውን እንደልብ ለመስራት ተቸገርኩኝ፡፡ አጋጣሚ ብድሩን አልወሰድኩኝም ነበር እና ሀሳቤን በመቀየር የልብስ ስፌት ስራውን በመተው የቤት ውስጥ እና የስጦታ እቃዎች መሸጫ ስራ ተሰማራሁ፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ተከራይቼ የምሰራበትን ህንፃ ውስጥ የአክሲዮን አባል ነበርኩኝ እና የሱቁን ኪራይ በቀላሉ ብዙም ሳልሰቃይ ለማግኘት ችያለሁ፡፡ ያው ሱቁን ያገኘሁት በኪራይም ቢሆን ማለት ነው፡፡ ወደ አዋጭ ከመግባቴ በፊት ከንግድ ስራውም ባሻገር ሌላ ስራ ነበረኝ፡፡ ባለቤቴ ጠበቃ ስለነበር ከእርሱ ጋር አብሬ እሰራ ነበር፡፡ ያው ስራው ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብዬ የምሰራው ስራ ነበር፡፡ ጥሩም ገቢ አገኝበት ነበር፡፡ ነገር ግን መቀመጡን ከጤናም አንፃር አልፈለኩትም ፤ የሚያንቀሳቅስ ልክ እንደ ንግድ አይነት ስራ እፈልግ ነበር፡፡ ለዛ ነው የቢሮውን ስራ ትቼ ወደ ንግዱ ዓለም ልቀላቀል የቻልኩት፡፡ ያው የንግዱን ስራ ከልጅነቴ ጀምሮ ስለምወደው ወደዚያ ስራ ለመቀላቀል ችያለሁ፡፡ አሁን ላይ ስራው ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን የንግድ ስርዓቱ እንደሚታሰበው ምቹ አይደለም፡፡ እንደልብ አያሰራም፣ ነገሮች በጣም እየናሩ ነው፣ እቃ ከምናመጣበት ቦታ ደረሰኝ አናገኝም፣ ያለደረሰኝ ስንሸጥ ቅጣት አለው፣ በደረሰኝ ስንሸጥ ደግሞ ደንበኞች እቃው ተወደደ ብለው ይላሉ በቃ ከመንግስት ጋር ሌባ እና ፖሊስ እንደመጫወት ነው፡፡ እንግዲህ እንደእነዚህ አይነት ነገሮች ትንሽ ቢከብዱም እኔ በስራዬ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ከራሴ አልፌ ደግሞ ለአራት ሰዎች የስራ እድል መፍጠር ችያለሁ፡፡

--

ወደ ህብረት ስራ ማህበሬ ከመምጣቴ በፊት ምንም የቁጠባ ልምድ የለኝም ነበር፡፡ አንዳንዴ ባንክ አስቀምጣለሁ፣ ህብረተሰቡ እንደሚያደርገው እቁብ እገባለሁ፡፡ ነገር ግን እኔ ከሁሉም በአዋጭ ቁጠባ ደስተኛ ነኝ፡፡ እስከዛሬ ድረስ አዋጭ ውስጥ ባለመቆጠቤ እስኪቆጨኝ ድረስ አዋጭ ላይ ወድጄ እና ፈልጌ በደስታ ነው የምቆጥበው፡፡ አዋጭ ውስጥ ቁጠባ መቆጠብ አባላት በአጭር ጊዜ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም የሚፈልጉትን ነገር በቀላሉ ማሳካት እንዲችሉ ይረዳል፡፡ እኔ ወደ ህብረት ስራ ማህበሩ ከመግባቴ በፊት ስለቁጠባ ያለኝ ግንዛቤ እንብዛም ነበር፡፡ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ሲባል ያጣ እና የተቸገረ ሰው ብቻ የሚጠቀምበት ተቋም ነበር የሚመስለኝ፡፡ የአዋጭ የአቆጣጠብ ስርዓቱ እራሱ የተቀመጠ ገንዘብ እንደልብ እንዳይወጣ እና እንዳይባክን ለማድረግ ይረዳል፡፡

አዋጭ ማለት ሰውን የሚጠቅም ብቻ ሳይሆን የሚያሳድግም ተቋም ነው፡፡ እኔ አባል ከሆንኩ በኋላ ወዲያውኑ ባለቤቴን እና ልጆቼንም ጭምር ነው ያስገባሁት፡፡ ከራሴ አልፌ እስካሁን በእኔ አማካኝነት ከአምስት በላይ ሰዎችን ህብረት ስራ ማህበሩን በአባልነት እንዲቀላቀሉ አድርጌአለሁ፡፡ ህብረት ስራ ማህበሬን ለሌሎች ሰዎች ሳስተዋውቅ ብዙ ሰዎች ይከፈልሻል ወይ ይሉኛል፡፡ አዋጭ በጣም እያደገ ያለ የህብረት ስራ ማህበር ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ መስራቾቹን እና ሰራተኞቹን በጣም ማድነቅ እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ከብዙ ሰው ጋር እየሰሩ እዚህ ስኬት ላይ መድረስ ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ በግሌ አውቀዋለሁ፡፡

ወደፊት ይህንን ስራ ትንሽ ከፍ ወዳለ ደረጃ ለምሳሌ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች መሸጫ አይነት ለማድረግ ትንሽ ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ምናልባት ስራውም ሰፋ ባለ ሁኔታ ቢሰራ ጥሩ ሊሆን የሚችል ይመስለኛል፡፡ አሁን ባለንበት ወቅት ያው ትግል ነው እንደምንም ላለመክሰር እንታገላለን እንጂ አመርቂ ትርፍ ይገኝበታል ብለን የምናስበው አይነት ስራ አይደለም፡፡

ለሌሎች ሴት እህቶቼ የማስተላልፈው መልእክት ምንድን ነው፡፡ ሴቶች ቤት አትቀመጡ እላለሁ፡፡ በአቅማቸው ወጥተው የሚችሉትን ስራ መስራት አለባቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ አንዳንዴ በኑሯቸው እና በትዳራቸው መሀል ችግር ተፈጥሮ በሚወጡበት ጊዜ ለአንድ ቀን እንኳን በልተው ማደር የሚችሉበትን ገንዘብ የሌላቸው በርካታ ሴቶች አሉ፡፡ ያገኙትን ስራ ሳይንቁ ቢሰሩ በተለይ ደግሞ አዋጭ ጋር መጥተው ቆጥበው እና ተበድረው አቅማቸው የቻለውን እና ውስጣቸው ያለውን ስራ እንደው ለምን ጉሊት መቸርቸር አይሆንም የትኛውንም ስራ መስራት ቢችሉ የተሻለ ነው ብዬ እላለሁ፡፡ መስራትም ይቻላል፡፡ ዋናው ነገር እሰራለሁ ብሎ ደፍሮ ከቤት መውጣቱ ነው ብዬ ለሴት እህቶቼ ማበረታት እፈልጋለሁ፡፡

አሁን ላይ እኔን በጣም ደስተኛ ከሚያደርገኝ ነገር መካከል ዋናው የራሴ ስራ አለኝ የሚለው ነገር ነው፡፡ በዚህ ደግሞ ትልቅ የሆነ የአይምሮ እርካታንም አግቼበታለሁ፡፡ ምንም ቢሆን አልጎዳም ምክንያቱም ተጠቃሚ ነኝ፣ የራሴ ገቢ አለኝ፣ በዛ ላይ ደግሞ የነጋዴ እጅ ላይ ገንዘብ አይጠፋም፡፡ አሁን እኔ እየሰራሁት ያለሁት መነሻ ነው፡፡ በዚህ እራሴን አልወስንም፡፡ ወደፊት ደግሞ ለስራዬ የሚረዳኝን የስራ መኪና ከአዋጭ ተበድሬ ለመግዛት እቅድ አለኝ፡፡

እውነትም አዋጭ እንደስሙ አዋጭ ነው፡፡ የሚያሳድግ እና ህይወትን የሚቀይር ተቋም ነው፡፡ ወደፊት አዋጭ ሰው ያሰበውን ትልልቅ ተቋማትን እንደ ፋብሪካ እና የተለያዩ ግዙፍ ድርጅቶችን ማቋቋም የሚያስችል እና ከሀገራችን አልፎ እስከ አፍሪካ ድረስ

ትልቅ ተቋም ሆኖ ማየትን እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ በርካታ ስለህብረት ስራ ማህበር ግንዛቤ ለሌላቸው ሰዎች ሰፊ የቅስቀሳ ስራ ያስፈልጋል የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡

በአዋጭ ሰራተኞች በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ብድር ለመውሰድ እራሱ አዲስ አበባ በሄድኩበት ጊዜ ወዲያ ነው የተስተናገድኩት፡፡ በጣም ትሁቶች ናቸው፣ በጣም ሰውን ማስተናገድ ይችላሉ፣ እያንዳንዱን ሰው ጎንበስ ቀና ብለው ነው የሚያስተናግዱት፡፡ ብዙ አባላት ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ዛሬም ነገም ሊጠይቋቸው ይችላሉ፡፡ ስራው በጣም አድካሚ ነው፡፡ ጠቅላላ ለአባላት በቃል የሚነገረውን ነገር ሁሉ በፅሁፍ መልክ ለአባላት መሰጠት ቢቻል የተሻለ ነው የሚል ግምት አለኝ፡፡ በተጨማሪም እኛ በቢሾፍቱ ከተማ የምንኖር የአዋጭ አባላት ብድር ሲሰጠንም እዚሁ ቢሾፍቱ ቅርንጫፍ ላይ ቢሆንልን ጥሩ ነው የሚል ጥቆማ አለኝ፡፡ ምክንያቱም ብዙ የስራ ጫና ሊቀንስልን ይችላል፡፡ በተጨማሪም በተሰማራንበት የስራ ዘርፍ ላይ ስልጠናዎች ቢመቻቹልንም በጣም ደስተኞች ነን፡፡

በመጨረሻም የህብረት ስራ ማህበራችንን ሰራተኞች በተለይ የቢሾፍቱ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ የሆነችውን ወ/ሮ ሔዋንን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ሰዎችን የምትንከባከብበትን እና የምታስተናግድበትን መንገድ በጣም ነው የምወደው፡፡ አንዳንዴ እኔ ትንሽ ቆጣ እላለሁ እና በዚያ ጊዜ ቆይ እስቲ እንደሱ እኮ አይደለም ብላ ታረጋጋኛለች፡፡ በአጠቃላይ እኔ አዋጭ ላይ ያሉ ሰራተኞች አቀራረፃቸው አንድ አይነት ነው መሰል ሁሉም ደስ የሚሉ እና አንድ አይነቶች ናቸው፡፡ ሁሉንም አመሰግናቸዋለሁ፡፡

© Awach SACCoS. All rights reserved
Website By: Alen Teshome