ወጣት ይድነቃቸው ሲያምረኝ

From
ቃሊቲ
አዋጭ ለእኔ ጓደኛዬ ነው

የወጣቶች የስራ ማጣት ችግር የበርካታ ሀገራት ራስ ምታት እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል፡፡ ለወጣቶች የተለያዩ የስራ እድሎችን በማመቻቸት ምርታማነታቸውን ማሳደግ የአንድን ሀገር ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግርን ለመፍታት ይረዳል ፡፡ በዓለማችን ከሚገኙ የአብዛኞቹን ሀገራት የስራ አጥ ቁጥር ስንመለከት የወጣት ስራ አጥ ቁጥር ከጎልማሳው የህብረተሰብ ክፍል ጋር ሲነፃፀር--በእጅጉ ከፍ ይላል፡፡ በርካታ ሀገራት ወጣቶች የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ቀጥታ ወደ ስራ ዓለም እንዲቀላቀሉ እና እራሳቸውን እንዲችሉ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን እና ፖሊሲዎችን ይቀርፃሉ፡፡ በተለይ እያደጉ ባሉ ሀገራት ላይ ወጣቶች ስራ የማግኘት ችግር ብቻ ሳይሆን ምቹ እና ተቀባይነት ያለውን ስራ የማግኘት ፍላጎት አላቸው፡፡ በሀገራችን ኢትዮጲያ ያለውንም ጉዳይ ስንመለከት የወጣቶች ስራ አጥነት ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣት በሀገራችንን እየተስተዋሉ ለሚገኙት የተለያዩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት በመሆን የስራ አጥ ወጣቶች ቁጥር መበራከት እንደ ትልቅ ተግዳሮት ሲጠቀስ ይስተዋላል፡፡ በተለይ በሀገራችን በገጠሩ ክፍል ወጣቱ ለመስሪያ የሚሆን ቦታ በማጣት ምክንያት የተለያዩ ስራዎችን ፍለጋ ወደ ከተማ ይፈልሳል፡፡ እንዲሁም በሀገራችን ከሚገኙ የተለያዩ የመንግስት እና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በየዓመቱ ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች አብዛኞቹ ስራ ፍለጋ በየማስታወቂያ ቦርዶቹ ላይ ሲንከራተቱ ይስተዋላሉ፡፡ ወጣቶች የስራ ፈላጊነት አስተሳሰብ ብቻ ይዘው እንዳይንቀሳቀሱ ያላቸውን ክህሎት፣እውቀት እና ሀሳብ ወደ ተግባር በመለወጥ ከተቀጣሪነት ባሻገር እንዲያስቡ በማስቻል በአቅማቸው ቆጥበው በመበደር ሀሳባቸውን ወደ ተግባር በመተርጎም ለራሳቸው ስራ በመፍጠር ቋሚ ገቢ እንዲያገኙ እንዲሁም ከራሳቸውም አልፈው ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር የሚችሉ ዜጋ እንዲሆኑ አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር ባለድርሻ አካል እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ ከስራዎቹም መካከል በተለይ ወጣቶች የራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የራሳቸውን መኪና ከህብረት ስራ ማህበሩ በሚመቻችላቸው ብድር አማካኝነት ገዝተው ወደ ስራ መሰማራት የሚችሉበትን መንገድ በማመቻቸት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያደረገ ይገኛል፡፡ለዛሬም ከህብረት ስራ ማህበራችን አባላት መካከል የወጣት ይድነቃቸው ሲያምረኝ ተሞክሮ በተለይ ለብዙ ወጣቶች ትምህርት ይሆናል ብለን ስላሰብን እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል፡፡ መልካም ንባብ እንዲሆንላችሁ ከወዲሁ ተመኘን፡፡

--

ስሜ ይድነቃቸው ሲያምረኝ ይባላል፡፡ በራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት ስራ ላይ ነው ተሰማርቼ የምገኘው፡፡ ወደዚህ አይነት ስራ ከመምጣቴ በፊት ተማሪ ነበርኩኝ፡፡ አሁን ላይ በቢዝነስ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪዬን አግኝቻለሁ፡፡ ትምህርቴን እንደጨረስኩ በፒካፕ መኪና የእቃ ትራንስፖርት አገልግሎት ስራ ላይ ተሰማርቼ ነበር እራሴንም የማስተዳድረው ቤተሰቦቼንም የምረዳው ፡፡ በዚህ መሀል በአንድ ወቅት አንድ የቅርብ ወዳጄ በአጋጣሚ ስለአዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበር አገልግሎት አጫወተኝ፡፡ ብዙም ጊዜ ሳላጠፋ አቅራቢያዬ ወደሚገኘው የአዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር ቅርንጫፍ ቢሮ በመሄድ ሙሉ መረጃ ከወሰድኩ በኋላ እና አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ በማሟላት የአዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር አባል ለመሆን ችያለሁ፡፡ በሂደትም ቁጠባዬን በየወሩ በተከታታይ በመቆጠብ የአዋጭ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኛለሁ፡፡ በወሰድኩትም ብድር 2001 ሞዴል ቪትዝ መኪና በመግዛት የራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት ስራ ላይ ልሰማራ ችያለሁ፡፡ አዋጭ ከገባሁ በኋላ ብዙ ለውጦች አሉኝ፡፡ ለምሳሌ ስራ አልነበረኝም አሁን ግን የራሴ ስራ ኖሮኛል፤ የቁጠባ ልምድ የለኝም ነበር ነገር ግን አሁን ጥሩ ቆጣቢ ለመሆን ችያለሁ፡፡ሌላው ከራይድ በፊት ስራ ስሰራ ስራው እራሱ በቴክኖሎጂ የታገዘ አልነበረም፣ በትክክል ገቢው እና ወጪው አይታወቅም ነበር፣ ምንም የተቀናጀ ነገር የለውም የያዝኩትን ይዤ ነበር የምገባው፣ ከአዋጭ ባገኘሁት ብድር የራይድ አገልግሎት ስራ ውስጥ ስገባ ግን አንደኛ ስራው ከቴክኖሎጂ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ወጪ እና ገቢዬን በአግባቡ እንድከታተል እና የቁጠባ ልምዴን እንዳዳብር አድርጎኛል፡፡ ወደ ህብረት ስራ ማህበሬ ከመግባቴ በፊት በፒክ አፕ ስራ ላይ ስሰማራ በአማካኝ በቀን ውስጥ ከስድስት መቶ እስከ ስምንት መቶ ብር ገቢ አገኝ ነበር፡፡ አሁን ላይ ከአንድ ሺህ ሁለት መቶ እስከ አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ገቢዬን ማሳደግ ችያለሁ፡፡

ወጣቱ ህብረተሰብ ከእኔ ጀምሮ የአመለካከት ችግር አለ፡፡ ህብረት ስራ ማህበራችን በ13.5 ፐርሰንት ብድር እየሰጠ ከሌሎች አበዳሪ ተቋማት በ17 ፐርሰንት ብድር የምንወስደው ነገር አለ፡፡ አብዛኛውን ሰው ስለ ህብረት ስራ ማህበር ብዙም እውቀት የለውም፡፡ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ደረጃ ብዙ ቢሰራ የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡ እኔ እራሱ አዋጭ ላይ ቁጠባ ስጀመር ብዙ ተቃውሞዎች ደርሶብኝ ነበር፡፡ በደንብ ሳታጣራ ዝም ብለህ እንዴት ትጀምራለህ የሚል እምነትን ከማጣት የመጣ ተቃውሞ እና ወቀሳ ከተለያዩ ሰዎች ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ ከገባሁ ስምንት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብድር አግኝቼ፣ የምፈልገውን ነገር አድርጌ ሲያዩኝ እኔን አይተው ወደ አምስት ስድስት ልጆች አባል የሆኑ አሉ፡፡ ስለዚህ ለሁሉም ወጣት የምመክረው ወደ አዋጭ ቢሮ በመምጣት ከተቋሙ ባለሙያዎች ትክክለኛ መረጃዎችን በመውሰድ አባል በመሆን ተጠቃሚ እንዲሆኑ እመክራለሁ፡፡ ብዙ ወጣቶች ጋር ብዙ አይነት ሀሳብ አለ፡፡ ያንን ሀሳብ ደግሞ ወደ ተግባር ለመቀየር የፋይናንስ ችግር ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ስለዚህ ወደ አዋጭ በመምጣት ሀሳባችንን ወደ ተግባር በመቀየር ያሰብናቸውን ነገሮች እናሳካ የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡

--

አዋጭ አባል ባልሆን ኖሮ በተማርኩበት ሙያ ስራ ለመፈለግ የትምህርት ማስረጃዬን ይዤ እዞር ነበር ማለት ነው፡፡ በየዓመቱ ከተለያዩ የግል እና የመንግስት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች አሉ፡፡ እንግዲህ እንደሀገር ይሔ በጣም ከባድ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን የራሴን ስራ መስራቴ ለእኔም፣ ለቤተሰብም እንዲሁም ለሀገር ከፍተኛ ጥቅም አለው ብዬ አስባለሁ፡፡ ሁልጊዜ መንግስት ያመቻቸውን የስራ እድል ብቻ መጠበቅ የለብንም፡፡ በራሳችን እየፈጠርን የምንሰራቸውም ስራዎች ሊኖሩ ይገባል፡፡

‹‹አዋጭ ለእኔ ጓደኛዬ ነው›› ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም የምፈልገውን ነገር እናዳሳካ የረዳኝ አዋጭ ነው፡፡ ለሌሎች እንደኔ ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ ቢመቻች ጥሩ ነው ባይ ነኝ፡፡ ሚዲያ ላይ እራሱ የአዋጭን ማስታወቂያ ብዙ ጊዜ አይታይም፡፡ በደንብ ሚዲያ ላይ ማስታወቂያ ቢሰራ እና ለህብረተሰቡ ተደራሽ ቢሆን ጥሩ ነው ባይ ነኝ፡፡

© Awach SACCoS. All rights reserved
Website By: Alen Teshome