አቶ አመሃ አማረ

From
ስላሴ
አዋጭ ለኔ የህይወት ምሰሶዬ ነው፡፡

በከተማችን አዲስ አበባ ላይ ያለውን የትራንስፖርት ችግር የሚቀንስ፣ የተሳፋሪውን ደህንነት እና ምቾት የሚጨምር እና በተሳፋሪ እና በአሽከርካሪ መሀከል ያለውን የዋጋ ክርክር የሚያስቀር ዘመናዊ ዲጂታል የኮንትራት ትራንስፖርት አገልግሎት ቴክኖሎጂ ከጥቂት ዓመታት በፊት በስፋት ተዋወቀ፡፡ ቴክኖሎጂው በተጨማሪ የተሳፋሪዎችን ደህንነት በተሻለ ማስጠበቅ መቻሉ እና በከተማችን ውስጥ ደንበኛው ካለበት ቦታ ሆኖ የትራንስፖርት አገልግሎቱን የእጁን ስልክ በመጠቀም ማዘዝ መቻሉ ለየት ያደርገዋል፡፡ በአንድ እና በሁለት ድርጅቶች ባለቤትነት የተጀመረው ይህ ስራ ዛሬ ላይ በአብዛኛው የከተማው ህዝብ ውስጥ በመታወቁ ምክንያት በርካታ ድርጅቶች አዋጭነቱን በማየት ዘርፉን በመቀላቀል ላይ ናቸው፡፡ ታዲያ ይህ ቴክኖሎጂ የተለያዩ ግለሰብ የመኪና ባለቤቶች ባላቸው እና በፈለጉት ጊዜ በኦንላይን ሲስተም በመግባት በራሳቸው መኪና በሹፍርና በመስራት በሰሩትበት ልክ ገቢ የሚያገኙበትን መንገድ ይዞ መምጣቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የመኪና ባለቤቶች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ አስችሏል፡፡ ታዲያ ህብረት ስራ ማህበራችን አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድርም በርካታ ለሆኑ አባላቶቹ አስተማማኝ እና ቀልጣፋ ብድርን ለአባላቱ በማቅረብ አባላት ተበድረው መኪና በመግዛት ዘርፉን እንዲቀላቀሉ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተጨማሪም በከተማችን እየታየ ላለው የትራንስፖርት ችግር መቃለል የበኩሉን አስተዋፅዖ አድርጓል፡፡ ለዛሬ ከህብረት ስራ ማህበራችን በወሰዱት ብድር የትራንስፖርት ዘርፉን በመቀላቀል ውጤታማ ከሆኑ ወጣት አባሎቻችን መካከል አቶ አማሀ አማረን ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ አቶ አመሃ በህብረት ስራ ማህበራሩ በተመቻቸለት ብድር አማካኝነት እንዴት ወደ ትራንስፖርቱ ዘርፍ በመግባት ውጤታማ ሊሆን እንደቻለ አጫውቶናል፡፡ ታሪኩም በተለይ በከተማችን ለሚገኙ በርካታ ወጣቶች ትምህርት ሊሆን ይችላል ብለን ስላሰብን እንደሚከተለው አዘጋጅተነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

እራስህን በማስተዋወቅ እንዴት ወደ አዋጭ እንደመጣህ አጫውተን ? ስሜ አመሀ አማረ ይባላል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ባለትዳር ነኝ፡፡ ትዳር ከመሰረትኩ ስድስት ወር ሞልቶኛል፡፡ ወደ አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበር ውስጥ አባል የሆንኩት ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ነበር፡፡ በወቅቱ የአዋጭ አባል እንድሆን ቴሌኮሚኒኬሽን የሚሰሩ ሰራተኞች ነበር ስለተቋሙ መረጃ የሰጡኝ፡፡

አዋጭ አባል ከመሆንህ በፊት ስለ አዋጭ ምን አይነት አመለካከት ነበረህ? ወደ አዋጭ ከመግባቴ በፊት ስለ አዋጭ ያን ያህል ጥሩ አመለካከት አልነበረኝም፡፡ በውስጤ የአለማመን እና የጥርጣሬ መንፈስ ነበረኝ፡፡ ህብረት ስራ ማህበር ሲባል ብዙ ሂደቶች ያሉት፤ ሰዎችን የሚያመላልሱ አለፍ ሲልም የሰዎችን ገንዘብ የሚያጭበረብሩ ነው የሚመስለኝ፡፡ ግን አዋጭ በፍፁም እንደዚህ አይደለም፡፡ አመላልሶኝ ወይም አጎሳቁሎኝ አያውቅም፡፡ አዋጭን እኔ እንደዚህ አገኘዋለሁ ብዬ አልጠበኩም ነበር፡፡ በእውነት አዋጭ ቃሉን ጠባቂ ነው፡፡ 6 ወር ቆጥባችሁ ብድር እሰጣችኋለሁ ካለ በትክክል ከ6 ወር ተከታታይ ቁጠባ በኋላ የብድር አገልግሎት ማግኘት ይቻላል ፡፡ የብድር አገልግሎቱን ለማግኘት ማሟላት የሚገባንን ነገር በቅድሚያ ይነግሩናል፡፡ በሚነግሩን መሰረት አስፈላጊውን መረጃ በሙሉ በሚገባ ካሟላን ያለምንም ችግር ነው የምንስተናገደው፡፡ አንዳንድ አበዳሪ ተቋማት ለትንሽ ብድር ብዙ ጊዜ ያመላልሱናል፡፡ ተስፋ ቆርጠን የብድር ሂደቱን እንድናቋርጥ ነው የሚያደርጉን፡፡ አዋጭ ላይ ግን እንደዚህ አይነት ነገር የለም፡፡

አዋጭን ከሌላ አበዳሪ ተቋም አንፃር እንዴት ታየዋለህ ? አዋጭ ከውጭ እና ከውስጥ ሆነው ሲያዩት በጣም የተለያየ ነገር ነው ያለው፡፡ እኔ ብዙ አበዳሪ ድርጅቶችን አውቃለሁ፡፡ እውነት እውነት ለመናገር አዋጭ ታማኝ እና ወጥ የሆነ ግልፅ አሰራር የሚሰራበት ተቋም ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከምንም በላይ አዋጭ ለኔ ከሌላ አበዳሪ ተቋም ይለይብኛል፡፡ አብዛኞቹ የግል ባንኮች ላይ ያለኝ ቅሬታ ቢኖር ሁሉም በሚባል ደረጃ ለባለሀብቶች የተቋቋሙ ናቸው፡፡ ያለንን ንብረትም አስይዘን ብድር ሊያበድሩን አልቻሉም፡፡ ፎቅ ካላቆመን፣ ኢንቨስትመንት ላይ ካልተሰማራን፣ አስመጪ እና ላኪ ካልሆንን እና ትላልቅ ንግድ ላይ ካልተሰማራን በስተቀር ለእንደኛ አይነት ከዜሮ ተነስቶ ለሚሰራ እና ለሚታትር ሰው በፍፁም አይሆኑም፡፡ ሁሌም የሚሉን ቆጥቡ ነው፡፡ ቆጥበን ግን ምን እንደምናደርግ አይነግሩንም፤ መልስም የላቸውም፡፡ እኔ በግሌ ሁሉም የግል ባንኮች 20 ዓመት የሞላቸውም ይሁን በዚህ 10 ዓመት ውስጥ የተመሰረቱት ጋር በሚባል ደረጃ ሄጄ ብድር ለማግኘት ሞክሬ ነበር፡፡ አንዳቸውም ግን እንደኔ ላለ ታዳጊ የሚያሰራ የብድር አሰራር በፍፁም የላቸውም፡፡ አዋጭ ግን ቆጥቡ እና ተበደሩ ነው እያለን ያለው፡፡ ይሄ በጣም ደስ የሚል ነገር ነው፡፡ አዋጭን ከዚህም በላይ ያድርግልን፡፡አዋጭ ችግሬን ሙሉ ለሙሉ እንድንቀርፍ፣ ከእግረኛነት ወደ ባለመኪናነት ፣ ከመኪናም ላይ ሌላ መኪና ጨምሬ 3ኛ መኪና እንድገዛ አድርጎኛል፡፡ አዋጭ ለኔ በእውነት እንደስሙ የሚያዋጣ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ተቋም ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በተጨማሪም አሁን ላይ ካለው የዋጋ ግሽበት አንፃር እንደድሮ መኪና እንደልብ እንድንገዛ ስለማያደርገን የብድር ጣሪያው ከፍ እንዲል ያቀረብነው ጥያቄ እነሆ መልስ አግኝቶ የ400ሺህ ብር የብድር ጣሪያ ወደ 600 ሺህ ብር ከፍ ብሎልናል፡፡ ለዚህም አዋጭን እጅግ በጣም እናመሰግናለን፡፡ እንደዚህ አይነት ታማኝ እና ቃሉን ጠባቂ የሆነ የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር እስካሁን አላየንም፡፡ ‹‹አዋጭ እንደስሙ አዋጭ ነው፡፡››

ስለ ቁጠባ ምን ትላለህ? የአዋጭ ዋነኛው ሀሳቡ ቁጠባ ነው፡፡ወጣት እንደመሆኔ መጠን በተለይ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ቁጠባ እንዴት መቆጠብ እንዳለበት ትንሽ ነገር ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ እኛ ወጣቶች እጃችን ላይ ብር ሲኖር ይጠፋል፤ የሆነ ነገር ያምረናል፡፡ ነገር ግን መንቃት መቻል አለብን፡፡ካለን ላይ መቆጠብ መቻል አለብን፡፡ ቁጠባ የስልጣኔ ምልክት ነው፡፡ ገንዘባችንን ባንክ ቤት ስናስቀምጥ በኤቲኤም ወይም በሌላ በተለያየ መንገድ ልናወጣው እንችላለን፡፡ አዋጭ ላይ ግን ስንቆጥብ የቆጠብነው ገንዘብ ከፍ እያለ ነው የሚመጣው፡፡ ትንሽ ቆጥቦ ብዙ ማትረፍ ይቻላል፡፡ ቁጠባ ማለት ከምናገኛት ገቢ ላይ የተወሰነ ነገር ቀንሰን ማስቀመጥ መቻል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በቀን አንድ መቶ ብር ገቢ የሚያገኝ ሰው ቢያንስ ሀምሳ ብር በየቀኑ ቢቆጥብ ፤ በተለይ ደግሞ አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር ላይ ቢቆጠብ የቆጠበው ቁጠባ ብድር ለመበደር ያስችለዋል ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ሰው በቀን አንድ መቶ ወይም ሁለት መቶ ብር ብቆጥብ በወር 3 ሺህ ወይም 6 ሺህ ብር ነው የሚሆነው እና በዛ ብር ምን ልሰራ እችላለሁ ይላል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ሀገራችን ውስጥ ብዙ ሰው ላይ ያለ አስተሳሰብ ነው፡፡ ብዙ ሰው ብር ተቆጥቦ ወይም ተጠራቅሞ ብቻ መኪና እና ቤት የሚገዛ ይመስለዋል፡፡ ነገሩ ግን እንደዛ አይደለም፡፡ ገንዘቡን በግላችን አጠራቅመን የምንፈልገውን ያህል ገንዘብ እስክንቆጥብ ድረስ መግዛት የምንፈልገው ነገር ዋጋው ከሚባለው በላይ እየናረ ይሄዳል፡፡

--

አዋጭ ላይ ያለህ የብድር ተሞክሮ ምን ይመስላል? የዛሬ አራት ዓመት በፊት አዋጭ ስመዘገብ ምንም ያልነበረኝ ሰው ነበርኩኝ፡፡ እቁብ ሰብስቤ ያገኘሁትን ገንዘብ አዋጭ ላይ በመቆጠብ እና የቁጠባ መጠኔን 50 ሺህ ብር በማድረስ በመጀመሪያ ዙር 200 ሺህ ብር ብድር አዋጭ ሰጠኝ፡፡ በዛች በወሰድኳት 200 ሺህ ብር ለመጀመሪያ ጊዜ የገዛኋት . ኮድ 2 ኤ 67775 የሆነች ዳማስ መኪና ነበረች፡፡ በዚህች ዳማስ መኪና ወደ ሁለት ዓመት አከባቢ ጠንክሬ መስራት ቀጠልኩኝ፡፡ ቀን ቀን እራሴ እንደሹፌር በመሆን መኪናዋን አከራያት ነበር፡፡ ማታ ማታ ደግሞ በዚህችው መኪና የእንቁላል ንግድ ስራ እሰራባት ነበር፤ የተለያዩ የለስላሳ መጠጦችን አከፋፍልበት ነበር፤ ለተለያዩ ኬክ ቤቶች እንዲሁ የተለያዩ ኬኮችን አከፋፍልበት ነበር፡፡ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን ስራውን ስጀምረው እንደዚህ ውጤታማ ያደርገኛል ብዬ አልጠበኩም፡፡ እየሰራሁ በማገኘው ገንዘብ ብድሬን ከፍዬ በመጨረስ እና ሁለተኛ ዙር ብድር በመውሰድ ሁለተኛ መኪናዬን ለመግዛት ሁለት ዓመት ብቻ ነበር የፈጀብኝ፡፡ ሁለተኛ ጊዜ ተበድሬ የገዛሁትንም ብድር በዓመቱ ነበር ሙሉ በሙሉ ከፍዬ የጨረስኩት፡፡ እኔ ሁልጊዜ አቅዳለሁ፡፡በእቅድ እና በዝግጅት ነው የምመራው፡፡ ሶስተኛ ዙር ብድር 400ሺህ በመውሰድ ሶስተኛ መኪናዬን መግዛት ችያለሁ፡፡ ቪትዝ መኪና ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ከመሸጫ ቤት 370 ሺህ ብር ነበር የሚሸጠው፡፡ እንግዲህ እኔ በወቅቱ 400 ሺህ ብር ብድር ወስጄ 370 ሺህ ብር ቪትዝ መኪና መግዛት ችያለሁ ማለት ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዳማሱን ሽጬ ቪትስ መኪና በመግዛት እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን በጠቅላላ የ 3 ቪትስ መኪና ባለቤት ለመሆን ችያለሁ፡፡ አንድኛውን መኪና እራሴ በመያዝ የራይድ እና የፈረስ ትራንስፖርት አገልግሎት ስራ እየሰራሁበት ሲሆን፤ ሁለቱን መኪኖች ደግሞ ስራ ለሌላቸው ወንድሞቼ በቀን ገቢ ሂሳብ መኪናውን ወስደው እየሰሩ እንዲጠቀሙበት ስራ ፈጥሬላቸዋለሁ፡፡

አዋጭን ለሌሎች ሰዎች እንዴት እያስተዋወክ ነው? እኔ በግሌ የራይድ እና የፈረስ ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች የሚገኙበት የማህበራዊ ትስስር ገፅ ቴልግራም ቻናል ላይ ገብቼ ቢያንስ በድምሩ 20ሺህ የቻናሉ ተከታዮች ስለ አዋጭ አስራር በግልፅነት ተናግሬ በርካታ ሰዎች ወደ አዋጭ መጥተዋል፡፡ በርካታ የሰው መኪና በመያዝ በቀን ገቢ የሚሰሩ ሰዎች የራሳቸውን መኪና ገዝተዋል፡፡ መኪና የነበራቸው ሰዎች ደግሞ ሌላ መኪና ደግመዋል፡፡ እኔ በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ እኛ ሀገር አንድ መጥፎ ባህል አለ፡፡ አንድ ድርጅት ወይም ግለሰብ ሲለወጥ የተለወጠበትን መንገድ ለሌሎች ሰዎች መናገር አይፈልግም፡፡ እኔ ግን ስለ አዋጭ ስናገር እጅግ በጣም ደስታ እየተሰማኝ ነው፡፡ የብዙ ወንድሞቼን መለወጥ እያየሁ እጅግ በጣም ኩራት እየተሰማኝ ነው፡፡ የወንድሞቼ መለወጥ የእኔም መለወጥ ነው ፡፡ የእኔም መለወጥ የእነርሱ መለወጥ ነው፡፡ እርስ በእርስ ተያይዘን ስናድግ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ በጣም ብዙ የራይድ እና የፈረስ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ወደ አዋጭ ገብተው ተጠቃሚ በመሆናቸው በጣም ያመሰግኑኛል፡፡ የህብረት ስራ ማህበራችን መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ሸለመ በጣም ላመሰግነው እወዳለሁ፡፡ በአንድ ሚዲያ ላይ ቀርቦ በአሁኑ ሰዓት ህብረት ስራ ማህበራችን ውስጥ ከአንድ ሺህ በላይ የሆኑ የኮድ 3 ተሸከርካሪ ባለቤት የሆኑ አባላት አሉ ሲል በጣም ነው ደስታ የተሰማኝ፡፡ በአሁኑ ሰዓት እኔ ባልሳሳት የአዋጭ አባላት ቁጥር ከ40ሺህ በላይ ሆኗል፡፡ በእርግጠኝነት እኔ በትንሹ በመቶዎች እና በሺህ ደረጃ የሚቆጠሩ አባላትን ወደ ህብረት ስራ ማህበሩ እንዲመጡ አድርጌአለሁ፡፡ እኔ በእውነት አዋጭን ከዚህም በላይ እፈትነዋለሁ፡፡ ከዚህም በላይ አባላትን ወደ ህብረት ስራ ማህበሩ አመጣለሁ፡፡ የበለጠ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲከፍት አደርጋለሁ፡፡ አድጎ ባንኮ ሆኖ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ አዋጭ ራዕያችንን እውን አድርጎልናል፡፡ ህይወታችንንም ለውጦልናል፡፡

--

አዋጭ ላይ ስላለው የብድር አገልግሎት ለሌሎች ሰዎች ምን ትላለህ ? በጣም ብዙ ሰዎች የአዋጭ ወለድ ስንት ነው እየሉ ይጠይቃሉ፡፡ በጣም ነው የሚገርመው፡፡ ይኼ ለኔ ትክክል ያልሆነ አስተሳሰብ ነው፡፡ እንደነገርኳችሁ እኔ ከሁለት ዓመት በፊት ቪትስ መኪና ስገዛ 370 ሺህ ብር ነው የገዛሁት፡፡ አሁን ላይ የቪትስ መኪና ዋጋ 700 ሺህ ብር ገብቷል፡፡ በዛ ላይ በሁለት ዓመት ውስጥ በራይድ እና በፈረስ ትራንስፖርት ስራ ስንት ብር ሰርቼበታለሁ የሚለውንም እንግዲህ አስቡት በትንሹ አራት መቶ እና አምስት መቶ ሺህ ብር ሰርቼበታለሁ፡፡ የመኪኖቼ ዋጋ በእጥፍ ነው የጨመረው፡፡ታዲያ ወለድ ብቻ ለምንድን ነው የሚታሰበው፡፡ አሁን ላይ የዛሬ ሁለት ዓመት በእኔ ጥቆማ 450 እና 460 ሺህ ብር መኪና የገዙ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ መኪኖቻቸው እስከ 650 እና 700ሺህ ብር እየተገመተላቸው ነው፡፡ ለዛውም መኪናውን ሰርተውበት ማለት ነው፡፡ በቀን በትንሹ 500 ብር ቢሰሩ በዓመት እስከ 200 ሺህ ብር ያገኙበታል፡፡ሌላው አብዛኛው ሰው የሚቸገርበት ጉዳይ የዋስትና ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ አዋጭ መፍትሄ አለው፡፡ አንድን ሊለወጥ የመጣ ተበዳሪ ግዴታ የቤት ካርታ እና የመኪና ሊብሬ አምጣ አይልም፡፡ እዛው አባል የሆነ ሰው በቁጠባ ዋስትና እንዲሆነው በማድረግ ብድር መውሰድ ይችላል፡፡ ብዙ ሰዎች ዋስትና ፍራቻ በመሸሽ ሳይመዘገቡ ይቀራሉ፡፡ ይህ ፈፅሞ ስህተት ነው፡፡ ሌላው አሁን ላይ አዋጭ ለአሰራር ቅልጥፍና ሲባል አዋጭ ብድሩን በየቅርንጫፍ ቢሮው መስጠት ጀምሯል፡፡ በፊት ላይ ዋናው ቢሮ ብቻ ነበር የሚሰጠው፡፡ አሁን ላይ በየቅርንጫፍ ቢሮ የብድር ስርጭት አገልግሎት መሰጠት መጀመሩ ከበፊቱ በጣም ባጠረ ጊዜ አባላቱ ሳይመላለሱ፣ሳይንከራተቱ እና ሳይሰቃዩ እንዲስተናገዱ ያስችላቸዋል ፡፡

አዋጭ አባል ከመሆንህ በፊት ስለነበረህ የስራ እና የገቢ ሁኔታ አጫውተን? አዋጭ አባል ከመሆኔ በፊት በርካታ ትላልቅ ሆቴሎች ላይ በኤሌክትሪሺያንነት ሙያ ተቀጥሬ ሰርቻለሁ፡፡ ግሎባል ሆቴል፣ ሲዮናት ሆቴል፣ሰሜን ሆቴል፣ ዴስቲኒ አዲስ ሆቴል፤ ቀነኒሳ ሆቴል፣ ሪሊያንስ ሆቴል እነዚህ በሙሉ ተቀጥሬ ከሰራሁባቸው ሆቴሎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ‹‹እኔ ስራ በጣም እወዳለሁ፡፡ ስራ ሱሴ ነው፡፡›› ሁለት ሶስት የተለያዩ ሆቴሎች ላይ በቀን ውስጥ እስከ 16 ሰዓት እስራ ነበር፡፡ አንዱ ጋር ምሽት፣አንዱ ጋር ቀን ፣ አንዱ ጋር አዳር እያደረኩ16 ሰዓት ሰርቼ በወር ውስጥ አገኝ የነበረው ደሞዝ ከ4 ሺህ እና ከ5 ሺህ ብር አያልፍም ነበር፡፡ ለዛውም የተለያዩ ሆቴሎች ውስጥ እራሴን ጎድቼ በቀን ውስጥ ለ16 ሰዓት ያህል ሰርቼ ማለት ነው፡፡በዛ ላይ ወርሀዊ ወጪውም ደግሞ የዛኑ ያህል ነው፡፡ የቤት ኪራይ አለ፣ቀለብ አለ፣ የተለያዩ ወጪዎች አሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ወደ ሰባት ዓመታት ያህል ተቀጥሬ ሰርቻለሁ፡፡ ነገር ግን ከተለመደው የዕለት ኑሮ ባለፈ ያን ያህል ህይወቴ ሊቀየር አልቻለም፡፡ መጨረሻ ላይ እስራበት ከነበረው ሆቴል ለቅቄ የራሴን ዳማስ መኪና ከአዋጭ ተበድሬ ከገዛሁ በኋላ መኪናዋ እየሰራች በምታመጣው ገቢ ወጪዋን ችላ በቀን ከ400 እስከ 500 ብር የተጣራ ትርፍ ማምጣት ጀመረች፡፡ እድሜ ለአዋጭ በዚህ ጊዜ ነበር በወር አስራ አምስት ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ህይወቴ መለወጥ የጀመረው፡፡

አሁን ላይ ጠቅላላ ወርሀዊ ገቢህ ምን ያህል ደርሷል? አሁን ላይ እኔ በያዝኩት መኪና በቀን ከ1000 እስከ 1500 ብር አገኛለሁ፡፡ በተጨማሪም በሁለቱ መኪኖች ደግሞ በቀን ገቢ 1000 ብር አገኛለሁ፡፡ በጥቅሉ አሁን ላይ በወር በአማካኝ እስከ 75 ሺህ ብር ወርሀዊ ገቢ አገኛለሁ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ከባለቤቴ ጋር ስንነጋገር በወርሀዊ ገቢ ደረጃ ከ5ሺህ ብር ወደ 75 ሺህ ብር መድረስ ማለት ለእኛ ትልቅ ስኬት እና ለውጥ እንደመሆኑ መጠን ሁሌ በዚህ ጉዳይ እንደነቃለን፡፡ አዋጭ ህይወታችንን ቀይሮልናል፡፡ አሁንም ከአዋጭ ጋር ብዙ እንጓዛለን፡፡ እኛም ህብረት ስራ ማህበራችንን እየፈተነው እንሄዳለን፡፡ መፈተን ለእኛም ለህብረት ስራ ማህበራችን አገልግሎትም በጣም ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ አዋጭም ያድጋል እኛም እናድጋለን፡፡ አዋጭ ከእኛ ፍላጎት ጋር እየተፎካከረ ሲያድግልን በዛው ልክ እኛም እያደግን እንሄዳለን፡፡

 

ብድር መበደርን ለሚፈሩ ሰዎች ምን መልዕክት አለህ ? አዋጭ ለሚያድግ እና ለሚለወጥ ሰው በትክክል የሚሆን ተቋም ነው፡፡ ልንሰራ ስለምንፈልገው ንግድ በቂ ጥናት ካደረግን፤ ብዙ አይነት የዋስትና አይነቶች ስላሉ ያለሀሳብ ብድር ማግኘት እና መጠቀም ይቻላል ማለት ነው፡፡ ‹‹አዋጭ ሰውን ይለውጣል፣ አዋጭ ያሳድጋል፡፡ ብድር ሰውን ይለውጣል፣ ብድር ሰውን ያሳድጋል፡፡›› አብዛኛው ሰው ብድር ሲባል በጣም ይፈራል፡፡ ንብረቴ በሀራጅ ሊሸጥብኝ ይችላል ብሎ ይሰጋል፡፡ ነገር ግን ብድር በጥናት እና በእቅድ ላይ ተመስርቶ ከተወሰደ እንደ ብድር ጥሩ ነገር የለም፡፡ ከተማችን ላይ የምናያቸው ባለሀብቶች በጠቅላላ በብድር ነው የሚሰሩት፡፡ አዋጭ እኛንም እዛ ደረጃ ላይ ያደርሰናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

አሁን ላይ ያለህን የኑሮ ደረጃ ስታይ ምን ይሰማሀል? አሁን ላይ ያለኝ ነገር ከአራት ዓመት በፊት ካለኝ ነገር ጋር ሳነፃፅረው እጅግ በጣም እደሰታለሁ፡፡ በእውነት ጥሬ ግሬ በላቤ ያመጣሁት ለውጥ ነው፡፡ አዋጭ በራስ መተማመኔን ከምንጊዜውም በላይ ከፍ አድርጎልኛል፡፡ ህብረት ስራ ማህበሬ ውስጥ ከመግባቴ በፊት በአስተሳሰብም ይሁን ኪሴ ውስጥ ባለው ገንዘብ ባለመተማመን ማድረግ እየፈለኩ የማላረጋቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ አሁን ግን እግዚአብሔር ይመስገን ከኔ አልፎ ቤተሰቦቼም ህይወቴ በሚታይ ደረጃ ተቀይሮ በማየታቸው ከኔ በላይ ደስተኞች ሆነዋል፡፡እድሜ ለአዋጭ አሁን ላይ የትኛውም ቦታ ላይ በመሄድ ደረቴን ነፍቼ ነው የፈለኩትን ነገር የማደርገው፡፡

ወደ ፊት ምን ለመስራት ታስባለህ? እኔ በግሌ በየዓመቱ ለማድረግ የማስባቸውን እቅዶችን ሁሌም መስከረም ወር ላይ እፅፋለሁ፡፡ ሁልጊዜ ሳቅድ ከአዋጭ ጋር አያይዤ ነው የማቅደው፡፡ ወደ ፊት እንደ ኤሌክትሪሺያንነቴ የኤሌክትሪክ እቃዎችን እያስመጣሁ ለመሸጥ እቅድ አለኝ፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ሰው የሚያውቀውን ስራ ነው መስራት ያለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡በሙያዬ ደግሞ ብሰራ የበለጠ ውጤታማ እሆናለሁ የሚል ግምት አለኝ፡፡

አዋጭን እንዴት ትገልፀዋለህ? ‹‹አዋጭ ለኔ የህይወት ምሰሶዬ ነው፡፡›› ቋሚ ነው፡፡ መቼም ቢሆን ውለታውን የማረሳው ባለውለታዬ ነው፡፡ አሁን ላለሁበት ደረጃ ያደረሰኝ ዋነኛ ቀኝ እጄ ነው፡፡

ወጣት እንደመሆንህ መጠን ለእድሜ እኩዮችህ ምን ትመክራለህ? ሀገራችን ላይ አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ወጣት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአብዛኛውን ወጣት ባህሪ እና ሁኔታ ወጣት እንደመሆኔ መጠን እረዳዋለሁ፡፡ አብዛኛው ወጣት በአጭር ማደግ ነው የሚፈልገው፡፡ ለማደግ መልፋት ያስፈልጋል፡፡ ወጣትነት የመስሪያ ጊዜ ነው፡፡ ትንሽ መልፋት ያስፈልጋል፡፡ ወጣቶች ብንቆጥብ መለወጥ ይቻላል፡፡ የአንድ ሚሊየን ብር ቤት ለመግዛት አንድ ሚሊየን ብር አያስፈልግም 30 ፐርሰንቱን አዋጭ ላይ ቆጥቦ በመበደር ቤት መግዛት ይቻላል፡፡

ማመስገን የምትፈልገው አካል ካለ? ማመስገን የምፈልገው ሰው አለ፡፡ ስራ አስኪያጃችን አቶ ዘሪሁን እሱ አያውቀኝም እኔ ግን አውቀዋለሁ፡፡ በእውነት በጣም በጣም መመስገን አለበት፡፡ ለብዙ ሰዎች መለወጥ ምክንያት ሆኗል፡፡ እሱ የዘረጋው አሰራር ብዙ ሰዎችን ጠቅሟል፡፡ እሱ ያሰበው ነገር እንዲሳካ እኔም የበኩሌን በርካታ ሰዎች ወደ አዋጭ እንዲመጡ እና ህልማቸውን እውን እንዲያደርጉ አስችያለሁ ፡፡ በተጨማሪም ዋናው መስሪያ ቤት ላይ ብድር ክፍል ያሉትን ሰራተኞች በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ በተለይ ወ/ሮ የምስራች እና ወ/ሮ ዮርዳኖስን በጣም ነው ማመስገን የምፈልገው፡፡ በጣም ደስ በሚል ሁኔታ እና በፈገግታ ነው የሚያስተናግዱን አንድ ቀን ሰው ሲያስኮርፉ እና ሲያስቀይሙ አይቼ አላውቅም፡፡ ሰው ደጋግሞ እንኳን ሲጠይቃቸው ቀስ ብለው ተረጋግተው ነው የሚያስተናግዱት እና እነሱን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡

--

በመጨረሻ የምትለው ነገር ካለ? አዋጭ ወደ ፊት ትልቅ ባንክ እንዲሆን ነው የምፈልገው፡፡ አብዛኛውን ሰው ስለ ህብረት ስራ ማህበራት ብዙ ግንዛቤ የለውም፡፡ አዋጭ በደንብ ማስታወቂያ መስራት እና ብዙ አባላትን ማምጣት መቻል አለበት፡፡ አዋጭ የሰውን ህይወት ለመለወጥ ትልቅ አማራጭ መሆኑን አብዛኛው ሰው አያውቅም፡፡ ስለዚህ በተለያዩ ሚዲያዎች እና ሶሻል ሚዲያዎች ላይ እራሱን ማስተዋወቅ ይጠበቅበታል፡፡

© Awach SACCoS. All rights reserved
Website By: Alen Teshome