ወ/ሮ ንፁህ አስረስ

From
አዲሱ ገበያ
እኔ ጋር በቁጠባ ቀልድ የለም

እንደ ዮኤስኤድ ገለፃ ከሆነ በሀገራችን 80% የሚሆነው የህብረተሰባችን ክፍል ከከተማ ውጭ እንደሚኖር እና በገጠር አከባቢ የሚደረገውን አብዛኛውን የግብርና ስራ በሴቶች እንደሚከናወን ይገልፃል፡፡ እንዲህም ሆኖ ሴቶች ለማህበረሰቡ እያደረጉ ያሉት አስተዋፅዖ በቅጡ እንኳን ሲታይላቸው አይስተዋልም፡፡ ኋላ ቀር በሆነ ባህል ሰበብ በአባቶቻቸውና በባሎቻቸው በተለያየ መንገድ የሀብት ተጠቃሚም ሆነ ተካፋይ እንዳይሆኑ ይደረጋሉ፡፡ ከማጀት አልፈው የተለያዩ ማህበራዊ ተሳትፎዎችን እንዳያደርጉ ይታገዳሉ፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ በሀገራችን ከሶስት ሴቶች ውስጥ አንድ ሴት አካላዊ፣ ስነልቦናዊ ወይም ፆታዊ ጥቃት ይደርስባታል፡፡ 65% የሚሆኑ ሴቶች ኋላ ቀር እና ጎጂ ልማዳዊ ባህል በሆነው የሴት ልጅ ግርዛት ሰለባ ሆነዋል፡፡ ከአንደኛ ደረጃ ሴት ተማሪዎች ውስጥ ግማሾቹ ብቻ እስከ አምስተኛ ክፍል ይደርሳሉ፡፡ ሴቶች ከወንዶች በባሰ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ይጋፈጣሉ፡፡ ህብረት ስራ ማህበራችን አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ሴቶችን የተለያዩ ገቢ የሚያስገኙ ስራዎችን በመፍጠር ወደ ንግዱ ዓለም እንዲቀላቀሉ እና ኑሮአቸውን በተሻለ መልኩ እንዲመሩ በማስቻል ሴቶች በሁለንተናዊ መልኩ በማብቃት ከወንዶች እኩል ወጥተው በመግባት እራሳቸውን፣ቤተሰባቸውን ብሎም ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ በማሰብ ለሴቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ከማሳያዎቹ ውስጥ ህብረት ስራ ማህበሩ ከምስረታው ጀምሮ ሴቶችን ባሳተፈ መልኩ መመስረቱ እና ከ41 የህብረት ስራ ማህበሩ መስራች አባላት ውስጥ ሰላሳ ሶስቱ ሴቶች መሆናቸው፤ ከህብረት ስራ ማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ተወካዮች ምክር ቤት አንስቶ እስከ ቅጥር ሰራተኞች ድረስ ሴቶችን በስፋት ያሳተፈ መሆኑ፤ ሴቶች ከቤት ወጥተው በንግዱ አለም በመሳተፍ የዳበረ ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲኖራቸው ለማበረታታት የብድር ወለድ መጠን ቅነሳ ማድረጉ ከብዙ በጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ለዛሬ በአዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበር አባል ከሆኑ እና የንግዱን ዓለም ተቀላቅለው በመስራት የራሳቸው የሆነ የገቢ ምንጭ ከመፍጠር ባለፈ ቤተሰባቸውን ማስተዳደር የቻሉ ሴት እንስቶች መካከል ወ/ሮ ንፁህ አስረስን ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡

/ሮ ንፁህ አስረስ የተዋጣላቸው ጎበዝ የመጋረጃ እና የተለያዩ ጨርቆች ስፌት ባለሙያ ናቸው፡፡ የስፌት ስራን ክፍለ ሀገር እያሉ ከልጅነታቸውን ጀምሮ በእጃቸው ጥልፍ እየጠለፉ በመሸጥ እንደጀመሩ ይናገራሉ፡፡ ሙያቸውን ከልምድ ባሻገር በትምህርት በማሳደግ በሙያው ከ18 ዓመት በላይ እንዳሳለፉ ይናገራሉ፡፡ ወ/ሮ ንፁህ በአንድ ወቅት ህብረት ስራ ማህበራችን አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር በአዲሱ ገበያ እርሳቸው የሚሰሩበት የስራ ቦታ አከባቢ ቅርንጫፍ ቢሮውን ሲከፍት መረጃ በማግኘት ህብረት ስራ ማህበራቸውን በአባልነት በመቀላቀል ቀጥለውም ለተከታታይ ወራት በመቆጠብ እና የብድር ተጠቃሚ በመሆን ከስፌት ስራ ባሻገር የተለያዩ ጨርቆችን እና መጋረጃዎችን አስመጥተው ወደ ማከፋፈል ስራ እንደተሸጋገሩ አጫውተውናል፡፡ ወ/ሮ ንፁህ ስለህይወት ተሞክሯቸው፣ ስለሙያቸው እና በአዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበር ውስጥ ስላላቸው የቁጠባና ብድር ተጠቃሚነታቸው በተለይ ለሌሎች ሴት እህቶቻችን አስተማሪ ነው ብለን ስለሰብን እንደሚከተለው አዘጋጅተነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

እራስሽን በማስተዋወቅ እንዴት ወደ አዋጭ እንደገባሽ አጫውችን ? /ሮ ንፁህ አስረስ እባላለሁ፡፡ አዲሱ ገበያ አከባቢ ነው የምኖረው፡፡ ባለትዳር እና የሶስት ሴት ልጆች እናት ነኝ፡፡ ስራዬ የልብስ ስፌት እና ሽያጭ ነው፡፡ በዚሁ ሙያ ነው ልጆቼን የማስተዳድረው፡፡ የአዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበር አገልግሎትን ለማወቅ የቻልኩት አዋጭ አዲሱ ገበያ አካባቢ ቅርንጫፍ ቢሮ የከፈተ ጊዜ የቅርንጫፍ ቢሮው ሰራተኞች የሆኑት እነ ወ/ሪት ሔርሞን በየሱቁ እየዞሩ ስለአዋጭ ዓላማ እያስረዱ ባሉበት ጊዜ ነው፡፡ በወቅቱ ሀሳቡን በሚገባ ተረድቼ እና ወድጄ ነው የህብረት ስራ ማህበሬን ልቀላቀል የቻልኩት፡፡ አዋጭ አባል ሆኜ ስመዘገብ እኔ ብቻ አይደለም የተመዘገብኩት ለልጆቼም ጭምር ነው የልጆች ቁጠባ ሂሳብ የከፈትኩት፡፡

--

ወደ አዋጭ ከመምጣትሽ በፊት ስለህብረት ስራ ማህበር ያለሽ አመለካከት ምን ይመስላል? አዋጭ ውስጥ ከመግባቴ በፊት ስለ ህብረት ስራ ማህበር ምንም አይነት ግንዛቤው አልነበረኝም ነበር፡፡ አዋጭ ከገባሁ በኋላ እና በህብረት ስራ ማህበሩ የሚሰጡ የተለያዩ ስልጠናዎችን ከወሰድኩ በኋላ አሁን ላይ ስለ ህብረት ስራ ማህበር ጥሩ ግንዛቤ አለኝ፡፡

----

የቁጠባ ልምድሽን አጫውችን ? እኔ ጋር በቁጠባ ቀልድ የለም፡፡ ሲጀመር በቁጠባ በጣም የማምን ሰው ነኝ፡፡ የንግድ ዓለም ላይ ቁጠባ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ቁጠባ ከሌለ ለውጥ የለም፡፡ ከአላስፈላጊ ወጪ መቆጠብም ቁጠባ ነው፡፡ እኛ ቤት አላስፈላጊ የሚባል ወጪ የለም፡፡ ሁሉም ነገር በእቅድ ነው የሚወጣው ፡፡ ለምሳሌ መርካቶ ስሄድ ለራይድ እና ለታክሲ ስንት ብር ነው የማወጣው ብዬ አገናዝቤ ነው የምወጣው፡፡ አንዳንዴ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ መርካቶ እቃ ሳመጣ ከኮንትራት መኪና ይልቅ በኖርማል ታክሲ ይዤ ልመጣ እችላለሁ፡፡ ወጪ ለመቀነስ ማለት ነው፡፡ ቁጠባ ከዚህ ነው የሚጀምረው፡፡ እኔ ህይወት ውስጥ ብር ስላለኝ ብቻ አንስቶ ግዢ የሚባል ነገር የለም፡፡ ለራሳችን ለኑሮ ዘይቤአችን እንኳን አንድ ችግር ቢመጣ ቀድሞ የሚደርስልን ቁጠባችን ነው፡፡ ገንዘብ ስላለን ብቻ እንደልባችን የምንሆን ከሆነ ከወረቱ ስንቁ እንደሚባለው ተረት ነው የሚሆነው ፡፡ ቁጠባ ለማንኛውም ሰው አስፈላጊ ነው፡፡ ሰው ሁሉ ከእኔ አቆጣጠብ እንዲማር እፈልጋለሁ፡፡ ልጆቼን እራሱ ቤታችን ላይ ስለቁጠባና ብድር የማሳያቸው ብዙ ነገር አለ፡፡ለሁሉም ልጆቼ በአዋጭ የገ///ኃላ/የተ/መሰ/የህ//ማህበር የልጆች ቁጠባ አካውንት ከፍቼላቸኋለሁ፡፡ አንድ ሰው ገንዘብን ቆጥቦ እንጂ ዝም ብሎ ከየትም እንደማያገኝ አስረዳቸዋለሁ፡፡ የእኔ የአቆጣጠብ ሁኔታ ትንሽ ለየት ይላል፡፡ ለስድስት ወራት ለእኔም ለልጆቼም ከቆጠብኩኝ በኋላ የቆጠብኩትን ገንዘብ ወደ ሼር/ዕጣ/ ባዞረው የተሻለ ትርፍ ክፍፍል በማግኘት ተጠቃሚ እንደምሆን በደንብ እየገባኝ ሲሄድ ያለኝን ቁጠባ ወደ ሼር/ዕጣ/ አዞርኩት፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለስራ ማስኬጃ የሚሆን ብድር ፈልጌ ስጠይቅ ባለኝ የቁጠባና እና አክሲዮን ገንዘብ መሰረት በእውነት ያለምንም ችግር ነው ብድሩን የሰጡኝ፡፡ ዓመታዊ የትርፍ ክፍፍል ላይም ጠርተው የትርፍ ክፍፍል ድርሻዬን ሰጥተውኛል ፡፡ በዚህም እጅግ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡

አዋጭ ላይ ያገኘሽው የብድር አገልግሎት ምን ይመስላል ? አዋጭ ከገባሁ በኋላ ለተከታታይ 6 ወራት ከቆጠብኩ በኋላ አንድ መቶ ሺህ ብር ብድር ወሰድኩኝ፡፡ በወሰድኩትም ብድር ከምሰራው የስፌት ስራ በተጨማሪ የተለያዩ የመጋረጃ እና የአልጋልብስ ጨርቆችን እያስመጣሁ መሸጥ ጀመርኩኝ፡፡ በድጋሜ አንድ አመት ከቆየሁ በኋላ በወሰድኩት ብድር ላይ ተጨማሪ ሰላሳ ሺህ ብር ብድር በመውሰድ እየሰራሁ ላለሁት የንግድ ስራ ማስኬጃ አዋልኩት ፡፡ አሁን ላይ ሱቄ ውስጥ አስገብቼ የማላውቀውን እቃ ነው አስገብቼ እየሸጥኩ ያለሁት፡፡

አዋጭ ከገባሽ በኋላ በስራሽ ላይ ስላመጣሽው ለውጥ እስኪ አጫውችን ? ከአዋጭ ብድር ከመውሰዴ በፊት የተለያዩ ጨርቆችን እየሰፋሁ እሸጥ ነበር፡፡ አዋጭ ውስጥ ከገባሁ በኋላ እራሴ እፈልጋቸው የነበሩ ስራዎችን መስራት ጀመርኩ፡፡ አሁን ላይ የተለያዩ ጨርቆችን በደርዘን እያመጣሁ መሸጥ ጀምሬአለሁ፡፡ የወሰድኩት ብድር ብዙ ጠቅሞኛል ብዙ መንገድን ከፍቶልኛል፡፡ መርካቶ አከባቢ ካሉ ጅምላ አከፋፋይ ነጋዴዎች ጋር ትስስር ፈጥሬ እንድሰራ አድርጎኛል፡፡ አሁን ላይ አዋጭ ስራዬን በምፈልገው ፍጥነት እየሰራሁ የምፈልገውን አካሄድ እንድሄድ አድርጎኛል፡፡ እኔ ለአዋጭ ትልቅ ቦታ አለኝ፡፡

የአዋጭን አገልግሎት ከሴቶች አንፃር እንዴት ታይዋለሽ ? በሴት ልጅ ውስጥ ሁሉም ነገር አለ፡፡ ቤተሰብም አለ፣ሀገርም አለች፡፡ ለዚህ ደግሞ እኔ እራሴ አንድ ምሳሌ ነኝ፡፡ በእኔ ውስጥ ብዙ ነገር እንዳለ አምናለሁ፡፡ ብዙ ቤተሰብ አስተዳድራለሁ፤ ብዙ ሴቶችን መንገድ አሳያለሁ እመራለሁ፡፡ ብዙ ሴቶችንም ወደ ህብረት ስራ ማህበሬ አስገብቻለሁ፡፡ አንድ ሴት አንድ ቦታ ላይ ገባች ማለት እንደ ቤተሰብ መሪነቷ ብዙ ነገርን መስራት ትችላለች ማለት ነው፡፡ ህብረት ስራ ማህበራችን አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላ/የተ/መሰ/የህ//ማህበር ብድር ስንበደር ለእኛ ሴቶች የተወሰነ የወለድ ቅናሽ አድርጎልናል፡፡ አበረታቶናል፡፡ በተለያየ ጊዜ በህብረት ስራ ማህበራችን እየተዘጋጀ የሚሰጠው ስልጠና ሴቶች ዓላማችን ፅኑ እንዲሆን አድርጎናል፡፡ ከእኔ አልፎ ዓላማው ገብቷቸው ወደ ህብረት ስራ ማህበራችን የገቡ ሴቶች ጓደኞቼ እንኳን ብዙ ሰዎችን ወደ ህብረት ስራ ማህበራችን አስገብተው የተለያዩ ስራዎችን እየፈጠሩ እና እያስፋፉ አሁን ላይ አብዛኞቹ ሴቶች ቤተሰብ እየመሩበት ነው፡፡ ትላንት እንኳን ብድር የወሰዱ ሁለት ሴቶች እኔ ጋር መጥተው እንዴት አድርገው እየሰሩ ብድራቸውን መመለስ እንዳለባቸው እየተወያየን ነበር፡፡ ሴቶች ራዕያችን እየሰፋ ነው ያለው፡፡ ከቁጠባና ብድር አገልግሎት ባለፈ የተለያዩ ምክሮችን ለማግኘት ወደ ህብረት ስራ ማህበራችን ቢሮ ብዙ ጊዜ እንሄዳለን፡፡ ሴትነታችን በጓዳ ብቻ እንዳይቀር እና ወጥተን እንድንሰራ፤ ለምንሰራው ስራ መነሻ እና ማስፋፊያ ብድር ደግሞ ህብረት ስራ ማህበራቸን ብድር እንደሚያመቻችልን በየጊዜው ይነገረናል፡፡ ብድርም ስንፈልግ የብድር አቅርቦቱ በቶሎ ነው የሚመቻችልን፡፡ ሴት ልጅ እንደ ወንድ ሁሉ አላማ እንዳላት እና ግብ ላይ መድረስ እንደምትችል እየተመካከርን ብዙ አስተዋፅዖ ነው እያተደረገልን ያለው፡፡ ሴትነት ኩራት ነው፡፡ ሴትነት እድገት ነው፡፡ በእኔ አመለካከት አንድ ቤተሰብ የተስተካከለ ነገር አለው መስመር ይዟል ከተባለ በእዛ ቤት ውስጥ አንድ ሴት ልጅ አለች ማለት፡፡ ምክንያቱም እኔ አንዷ ምሳሌ ስለሆንኩ ማለት ነው፡፡ ሴት ልጅ እቤት ውስጥ መዋል የለባትም፡፡ ከቤት የወጣን ሴቶች ቤት ውስጥ የቀሩትን ሴቶች ማውጣት እና ማሰራት አለብን፡፡ ሴት ልጅ ስትሰራ ልጇን በጥሩ ሁኔታ ታሳድጋለች፡፡ ለትዳር አጋሯም በኢኮኖሚው ዘርፍ አጋዥ ትሆናለች፡፡

ስለራስሽ የህይወት ተሞክሮ አጫውችን ? እኔ በጣም ታጋይ ሴት ነኝ፡፡ ማንኛውንም ስራ አልንቅም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ማንኛውንም ስራ ለመስራት ዝግጁ ነኝ፡፡ ሰው ከሰራ እንደሚለወጥ በጣም የማምን ሰው ነኝ፡፡ ከመነሻዬ ጀምሮ በስራ አምናለሁ፡፡ ሰርቼም እንደምለወጥ እርግጠኛ ነኝ፡፡ በዘመኔ ሁሉ ከማንም እጅ ላይ ዝቅ ብዬ አላውቅም፡፡ ይሄ ስራ ትንሽ ነው ወይም ትልቅ ነው ብዬ አላውቅም፡፡ ዝቅ ብዬ እሰራለሁ፡፡ አብዛኛውን ጊዜዬን በስራ ስለማሳልፍ መንገዴ የተቃና ነው፡፡ እኛ ሴቶች ላይ በእርግጥ ብዙ ውጣ ውረዶች አሉ፡፡ እርግዝና አለ፣ መውለድም አለ፡፡ በዛ ሁሉ መሀል ግን ሴቶች ምንድን ነው ማድረግ ያለብን? ምንድንስ ነው መስራት ያለብን? ብለን ባለራዕይ መሆን አለብን፡፡ እኔ ምንም ቀን አላባክንም አርግዤም ይሁን ወልጄ አራስ ቤት ሆኜ ስራዬን አስተካክዬ ነው የምቀመጠው፡፡ ባለሁበት ቦታ ሆኜ ስራዎቼን እቆጣጠራለሁ፡፡ ከባድ ፈተና ነው የተባለ ህይወት ለእኔ መንገድን የያዘ ነው፡፡ እንደኔ አስተሳሰብ ሴት ልጅ ከሰራች ከባድ የሚባል ነገር መጋፈጥ ትችላለች፡፡ እድሜያችንን እና ጊዜያችንን ከተጠቀምን ሁሉንም ነገር ማሸነፍ እንችላለን፡፡ ለስራ የሚታገል ሰው እና በእውነት ለቆመ ሰው ሁሉም ነገር ተዘጋጅቶ የተቀመጠ ነው፡፡ መንገዱ ሁሉ ክፍት ነው፡፡

አዋጭን ከሌሎች ተቋማት አንፃር እንዴት ታይዋለሽ? አዋጭ ከመምጣቴ በፊት ብድር እንስጣችሁ ብለው የሚመጡ ብዙ አበዳሪ ተቋማት ነበሩ፡፡ የስራ ቦታችን ድረስ እየመጡ ብድር እንስጣችሁ ይሉናል፡፡ ነገር ግን እኔ ደስ ብሎኝ አባል ሆኜ አላማው ገብቶች የተበደርኩት ከአዋጭ ነው፡፡

አዋጭን እንዴት ትገልጪዋለሽ? አዋጭ ለእኔ እግዚአብሔር ከፊት ለፊቴ ያመጣው በረከት ነው፡፡ ለእድገቴ ለውጥ ሆኖልኛል፡፡ አዋጭ ለእኔ ከእግዚአብሔር የተሰጠኝ ነው፡፡

አዋጭ በመግባትሽ ስላመጣሻቸው ለውጦች አጫውችን? አዋጭ ከገባሁ በኋላ ከፍተኛ የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥቻለሁ፡፡ አሁን ላይ ከንግዱ ባለፈ የራሴን ቤት ስለመግዛት እና ለስራዬ የሚረዳኝን መኪና ስለመግዛት ነው የማስበው፡፡ ህብረት ስራ ማህበሬ በቆጠብኩት መጠን እንደሚያግዘኝ ገብቶኛል፡፡ ያለምንም ችግር ራዕዬ ከፍ እያለ እንደሚሄድ ነው የሚሰማኝ፡፡

/ሮ ንፁህ ከአዋጭ የብድር ተጠቃሚ ባትሆን ኖሮ አሁን ላይ ምን አይነት ደረጃ ላይ ትሆን ነበር? እኔ ከአዋጭ ብድር ባላገኝ ኖሮ አሁን ላይ የተለያዩ እቃዎችን እንዲህ በደርዘን እያመጣሁ መሸጥ አልችልም ነበር፡፡ በኖርኩበት የስፌት እና የሽያጭ ስራ ነበር የምቀጥለው፡፡ ጊዜዩንም በዛ ነበር የምፈጀው፡፡ የህብረት ስራ ማህበሬ ብድር ነው ወደ ሌላ ራዕይ እንድሄድ የረዳኝ፡፡

የወደፊት ራዕይሽ ምን ይመስላል ? በቀጣይ ከህብረት ስራ ማህበሬ ከዚህ የተሻለ ብድር ቢመቻችልኝ፡፡ እኔ ወደ ጠቅላላ አስመጪነት ደረጃ ነው ማደግ የምፈልገው፡፡ ለዚህም ደግሞ ባለሙሉ ተስፈኛ ነኝ፡፡ ይህንን ስናገር ደግሞ በህብረት ስራ ማህበሬ ላይ በትክክል ተማምኜ ነው፡፡

ህብረት ስራ ማህበራችን ላይ ቢስተካከል ወይም ይሄ ቢደረግ ብለሽ የምትይው ነገር ካለ? ወደፊት አዋጭ ከአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ አልፎ ወደ በመላው ሀገራችን የሚገኙ የተለያዩ ክፍለ ሀገራት እንዲገባ እና ልክ እንደኛ በየክፍለ ሀገራቱ ያሉ ቤት ውስጥ የቀሩ ሴቶች እንዲጠቀሙ እና አዋጭ በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ ላይ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር እፈልጋለሁ፡፡

በመጨረሻ ማመስገን የምትፈልጊው ካለ? አዋጭ ውስጥ የሚሰሩትን ሰራተኞ በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ንግግራቸው እና አረዳዳቸው ህዝቡ እንዲገባ የሚያደርግ አግባቦት አለው፡፡ በአዲሱ ገበያ ቅርንጫፍ ቢሮ እነ ወ/ሪት ሔርሞንን እንዲሁም የህብረት ስራ ማህበሩ ዋናው ቢሮ ላይ ደግሞ ብድር ለመውሰድ ስንሄድ እነ ወ/ሮ ፀሀይን ብድር ልንወስድ ስንል ያደረጉት ትግል በተለይ ጊዜያችን እንዳይበላ ያደረጉትን ርብርብ ልረሳው አልችልም፡፡ በተጨማሪም የህብረት ስራ ማህበሩ የልጆች ቁጠባ ቀን ሲከበር አዋጭ ቆጣቢ ልጆችን አንድ ላይ ሰብስቦ ስለሚያዝናና እና ስለሚያስተምር በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ይህ ፕሮግራም ሲዘጋጅ እኔ ልጆቼን እና የጓደኞቼን ልጆች ሰብስቤ ነው የምሄደው፡፡ እንደውም ልጆቼ የዛሬ ዓመት እናቴ አመሰግንሻለሁ፡፡ እንደዚህ የተዝናናነው እንቺ ቁጠባ ስለጀመርሽልን ነው ብለውኛል፡፡ በዚህ ዓመት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት እስካሁን ይህ ፕሮግራም አልተዘጋጀም እና በዚህ አጋጣሚ እንድታስቡበት ለማለት ነው፡፡ በተረፈ ስለሁሉም ነገር እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ፡፡

© Awach SACCoS. All rights reserved
Website By: Alen Teshome